የሀረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የመንግስት ፋይናንስ ዘርፍ አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ አፈጻጸምን የሥራ ግምገማ መድረክ ከአብይ ኮሚቴ አባላት ጋር አካሄደ።
የስብሰባውን መድረክ በይፋ የከፈቱት የቢሮው ኃላፊ እና የአብይ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሐመድ ያህያ እንደገለጹት የፋይናንስ ሴክተር ሪፎርም በመንግስት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ፖሊሲዎች መሠረት ተቋማዊ አቅምን ለማጠናከር፣ የፋይናንስ አስተዳደርን ለማዘመን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማሳደግ እንዲሁም ውጤታማ የፋይናንስ ሥርዓት ለመገንባት የተጀመረ ወሳኝ የለውጥ ፕሮግራም ነው።
የቢሮው ኃላፊ አያይዘውም ይህ የሪፎርም ትግበራ የክልላችንን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን፣ ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል እና የመንግስትን ሀብት በብቃት ለመጠቀም ወሳኝ ሚና አለው። በተለይም አሠራራችንን በዲጂታላይዜሽን ማስደገፋችን ለዘመናዊ የፋይናንስ አስተዳደር ግንባታ የላቀ ፋይዳ ይፈጥራል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በመቀጠልም በቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ በአቶ ኑረዲን አማካይነት በዝግጅት ምዕራፉ እስካሁን የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የቀጣይ ሥራዎች አቅጣጫን ያካተተ ዝርዝር ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የአብይ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው የተዘጋጁ ሰነዶች በፍጥነት እንዲጸድቁ፣ የሚወጡ የሕግና የመመሪያ ማሻሻያዎች ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስፈላጊው ግብዓት ተሰብስቦ ሥራው እንዲጠናቀቅ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ያህያ አብዱራሂም በዝግጅት ምዕራፉ የተከናወኑ ሰነዶችና የቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።የሪፎርም ሥራው በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቅም የክትትልና ድጋፍ ሥራው እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።አያይዘውም በቀጣይ የዳይሬክቶሬቶች ቅንጅት የበለጠ ተጠናክሮ የተጀመሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ወደ ሙሉ ትግበራ ለመሸጋገር መስርት መጣል እንዳለባቸው አፅኖት ስጥቶዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የቢሮው ኃላፊ አቶ መሐመድ ያህያ በሰጡት የመዝጊያ ንግግር የቴክኒክ ኮሚቴው ያቀረበውን አጠቃላይ አፈጻጸምና በውይይቱ የተነሱ ገንቢ አስተያየቶችን አድንቀዋል።
በመጨረሻም ቢሮ ኃላፊው ይህ የሪፎርም ሂደት ለክልላችን ፋይናንስ ዘላቂነት፣ ለሀብት አጠቃቀም ውጤታማነት እና ለዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ የቢሮው አመራሮችና የሪፎርም አፈጻጸም ኮሚቴዎች የሪፎርሙን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት በታቀደላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ ሁሉም አካል በኃላፊነት ስሜት መስራት አለበት” ሲሉ ጥሪያቸውን በማቅረብ የመድረኩን ፍጻሜ አብስረዋል።











