ነሐሴ 6/2018 — በሀረሪ ክልል በየዓመቱ የሚካሄደው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰባችንን በርካታ ችግሮች እያቃለለ ይገኛል። የዚህ በጎ ተግባር አካል የሆነው የክልሉ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የሚሆኑ የትምህርት ቁሳቁሶችን በማዘጋጀት ለሀረሪ ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ማስረከቡን አስታውቋል።
በዕለቱ ከተደረጉት ድጋፎች መካከል 200 ደርዘን ደብተር እና 1,000 ፍሬ እስክሪብቶዎች ይገኙበታል። እነዚህ ቁሳቁሶች በአቅም ማነስ ምክንያት ለልጆቻቸው ደብተርና እስክሪብቶ ማሟላት ለሚቸገሩ ወላጆች ትልቅ እፎይታ የሚፈጥር ነው።
በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲያቋርጡ አለመፍቀድ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ድጋፎች ልጆች ያለ ስጋት እንዲማሩ ከማድረጋቸውም በላይ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችላቸውን ተስፋና ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው በስነ-ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል።
በመጨረሻም አንድም ልጅ በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ቤት እንዳይቀር በሚለው መርህ መሰረት የመንግስት፣ የባለሀብቱና የህብረተሰቡ ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑ ተስመሮበታል። በመሆኑም መሰል የወገን አለኝታነትን የሚያሳይ የበጎ አድራጎት ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ቢሮው ጥሪውን አስተላልፏል።







