የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ በሰው ተኮር አገልግሎት» በሚል መሪ ሃሳብ ለቢሮው ሠራተኞች እና አመራሮች የመንግስት ፋይናንስ ዘርፍ አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ማካሄዱን አስታወቀ።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የቢሮው ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ያህያ አብዱራሂም፤ ተቋማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የተገልጋዮች እና የባለድርሻ አካላት ፍላጎት ምላሽ እንዲሰጥ፣ አሰራሩን ከዘመኑ ጋር በማስተሳሰር እና በሰው ተኮር አገልግሎት የለውጥ ጉዞውን ለማፋጠን ስልጠናው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክትል ኃላፊው አክለውም ተቋሙ የቆየ ዕድሜና ልምድ ያለው ቢሆንም ከዕድሜው ጋር በተመጣጠነ እና ሕዝቡ በሚጠብቀው ልክ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ዘመናዊ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር የቆዩ የተጠራቀሙ ችግሮች፣ የሰው ኃይል አጠቃቀም ውስንነቶች፣ የአሰራር ችግሮች እና የመረጃ አያያዝ ክፍተቶች እንደነበሩ አንስተዋል። እነዚህን መሰረታዊ ስብራቶች ለመጠገን እና ዘላቂ የሜሪት (Merit-based) አሰራርን ለመዘርጋት አቅጣጫዎችን ነድፎ መንቀሳቀስ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም አበክረው አሳስበዋል።
የፋይናንስ አስተዳደር አገልግሎት ሰጪ እንደመሆኑ መጠን የቢሮው እንቅስቃሴ ለአጠቃላይ የክልላችን ልማትና መልካም አስተዳደር ስኬት የጀርባ አጥንት መሆኑን የገለጹት ም/ቢሮ ኃላፊ ስልጠናው ንድፈ-ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በሥራችን ውስጥ አሰራሮችን እንድንፈትሽ፣ ክፍተቶችን አርመን በቁርጠኝነት ወደ ተግባር እንድንገባ የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ከዝግጅት ምዕራፍ እስከ ተግባር ድረስ እያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራው ባለቤት በመሆን ሪፎርሙን በባለቤትነት ስሜት እንዲደግፍና ከተቋማዊ ግቦች ጋር የተናበበ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመድረኩም ከሪፎርም ኮሚቴው አባላት እና ከሰው ሀብትና ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ከተጋበዙ እንግዶች የተለያዩ ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ሰልጣኞችም ያነሷቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
የዕለቱ የመድረክ ውይይት በምክትል ቢሮ ኃላፊው ማጠቃለያ የተጠናቀቀ ሲሆን በሰው ተኮር አገልግሎት የሚለውን ራዕይ እውን ለማድረግ የጀመርነውን የሪፎርም ስልጠና ዛሬ ላይ ሆነን ስንመዝነው ትልቅ እርምጃ የተጓዝንበት እና ለቀጣይ ሥራ ትልቅ ግንዛቤ የጨበጠን ሆኖ ተገኝቷል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሀምሌ 16/2018














