የሐረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግሥት ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በማስመልከት “በብዝሃነት የደመቀች፣ በምክክር የጸናች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል፣ “የብዝሃነት አስተዳደርና የመንግሥታት ግንኙነት ለጠንካራ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታ” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።
መድረኩን በይፋ የከፈቱት የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ያህያ አብዱረሂም ብዝሃነት የሰው ልጆች የተፈጥሮ፣ የማኅበራዊ ኑሮና የባህል መገለጫ መሆኑን ገልጸው የቋንቋ፣ የባህል፣ የሃይማኖትና የእሴት ልዩነቶችን ጠብቆ በጋራ መኖር ለአንድ ሀገር ትልቅ ጸጋ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለጻ ውጤታማ የብዝሃነት አስተዳደር የዜጎችን እኩል መብትና ዕድል ከማረጋገጡም በላይ ሁሉም ዜጋ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የባለቤትነት ስሜት ኖሮት በእኩልነት እንዲሳተፍ ያስችላል። ብዝሃነትን በኃይል ለመጨፍለቅ ወይም ለማጥፋት መሞከር ወደ ግጭትና መበታተን ሊያመራ እንደሚችል በማስገንዘብ ልዩነቶችን አክብሮ የጋራ አንድነትን መገንባት አካታች አስተዳደርንና ጠንካራ የዴሞክራሲ ባህልን እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በደስታም ሆነ በሐዘን፣ በችግርና በውጭ ወረራ ወቅት በጋራ የኖረች፣ አንድነቷንም በአኩሪ ታሪክ ያስመሰከረች የብዝሃነት ሀገር መሆኗን ምክትል ቢሮ ኃላፊ አንስተዋል። ይህንን የብዝሃነት ጸጋ ወደ ዘላቂ ሰላም፣ የተረጋጋ ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማሸጋገር የፌዴራል ሥርዓቱን በትክክለኛ አቅጣጫ ማስኬድ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በተለይም ባለፉት ዓመታት የታዩ የፖለቲካ ባህል ውስንነቶችን፣ በብሔርና በመልክዓ ምድር ዙሪያ የሚከሰቱ ጽንፈኛ አመለካከቶችን እንዲሁም በመንግሥታት መካከል ባለው ተቋማዊ ግንኙነት የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ በምክክር፣ በመግባባትና በትብብር መሥራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
ቢሮው በበኩሉ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው የበጀት አስተዳደርን እንዲሁም ተቋማዊ ትብብርን በማጠናከር ለፌዴራል ሥርዓቱ ጥንካሬና መጎልበት የራሱን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል።
የውይይቱ ዋና ዓላማም በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በአስተምህሮ ማዕከሉ የተዘጋጀውን የውይይት ሰነድ መነሻ በማድረግ፣ በብዝሃነት አስተዳደርና በመንግሥታት ግንኙነት ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የፌዴራል ሥርዓቱን ለማጠናከርና በመድረኩ የተገኘው እውቀት በየሥራ ክፍሉና በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲሰፋ ማስቻል መሆኑን የውይይት ሰነዱን ያቀረቡት አቶ ኑረዲን መሐመድ አብራርተዋል።
በመቀጠልም በቀረበው ሰነድ ላይ ሰፊ ውይይትና ሃሳብ ልውውጥ ተካሂዷል። ተሳታፊዎችም በጉዳዩ ላይ ገንቢ ሃሳቦችን በማንሳት ያሉትን ጠንካራ ጎኖች ለማስቀጠልና ያጋጠሙ ፈተናዎችን በጋራ ለመሻገር የሚያስችሉ ሃሳቦችን አንስተዋል።
መርሃ ግብሩም ከውይይቱ በኋላ በተለያዩ የበዓሉ አከባበር ፕሮግራሞች ተጠናቋል።














